Community

ማህበራዊ ሕይወት

አንድ ክርስትያን ሌሎች ክርስትያኖች ያስፈልጉታል፡፡ በክርስትና ውስጥ ያለሌላው ክርስትያን ተሳትፎ መንፈሳዊ እድገት አይኖርም፡፡ እያንዳንዱም ክርስትያን ከሌላው የሚቀበለውና እራሱም ለሌላው ክርስትያን የሚሰጠው ጸጋ አለው፡፡ ምክንያቱም ክርስትያን የአካሉ (የቤተክርስትያን) አንድ ብልት ነው፡፡ በአካል ውስጥ አንድ ብልት ያለሌሎች ብልቶች ህይወት ሊኖረው አይችልም፡፡ ሌሎችም ብልቶች ይኸ ብልት ያስፈልጋቸዋል፡፡

የዓለምአቀፍ የኢተዮጵያ ወንጌላዊት ቤተክርስትያን መጽሐፍ ቅዱስ ኮሌጅ (IEECBC) ከምንም በላይ የተማሪዎቹን ክርስትያናዊ መንፈሳዊ ህይወት ለውጥና እድገት አጥብቆ የሚፈልግና ለዚህም የሚሰራ ነው፡፡ ከላይ የተጠቀሱትን መሰረት በማድረግ ተማሪዎች በእየአካባቢያቸው አነስተኛ ቡድኖችን እንዲያቋቁሙና በነዚህ ቡድኖች ውስጥ ሆነው እንዲፀልዩ፣ የእግዚአብሔርን ቃል እንዲከፋፈሉ፣ የቤት ስራቸውን እንዲወያዩበትና፣ ፈተናቸውን አብረው እንዲያጠኑ የመጽሐፍ ቅዱስ ኮሌጁ አጥብቆ ያበረታታል፡፡

በአካል ተገናኝተው አነስተኛ ቡድን ፈጥረው ከላይ የተጠቀሱትን ለማከናወን የማይችሉት ደግሞ ለምሳሌ አክል ከዚህ በታች የተጠቀሱትን ድህረ ገጾችና መገናኛዎችን በመጠቀም በእያሉበት ቦታ ሆነው ግን በጋራ እንዲፀልዩ፣ የእግዚአብሔርን ቃል እንዲከፋፈሉ፣ የቤት ስራቸውን እንዲወያዩበትና፣ ፈተናቸውን አብረው እንዲያጠኑ ይበረታታሉ፡፡

አንድ ሰው ሁልጊዜ በሁሉ ነገር ብርቱ አይሆንም፡፡ በመንፈሳዊ ህይወታችን የምንደክምበትና የምንወርድበት ጊዜአቶች አሉ፡፡ አነስተኛ ቡድኖች በምንወርድበት ጊዜ የሚያጽናኑንና የሚያበረታቱን፣ በመንፈሳዊ ሁኔታችን ብርቱ በሆንበት ጊዜ ደግሞ ጸጋችንን የምናካፍልበት፣ ሌሎችን የምናበረታታበትና ካሉበት ጉድጓድ እንዲወጡ መሰላል የምንሆንበት ይሆናል፡፡ እንዲህ ስንሆን በወንድሞቻችንና በእህቶቻችን ላይ የምንጠቋቆምና ፈራጆች አንሆንም፡፡

እነዚህ አነስተኛ ቡድኖች ማህበራዊ ህይወታችንንም የምናስተሳስርባቸው ልናደርጋቸው አንችላለን፡፡ ለምሳሌ በመልካም ጊዜ የደስታ ተካፋዮች የምንሆንበት በበሽታና በሃዘን ጊዜ ደግሞ ለበሽተኛው አጥብቀን የምጸልይበት፣ ሃዘንተኛውን የምናጽናናበትና ሸክሞችን የምንጋራበት ሊሆኑ ይችላሉ፡፡

ካለው ልምድ ተነስተን እነዚህ በተማሪዎች የሚቋቋሙ አነስተኛ ቡድኖች አባሎች ቁጥራቸው ከ አስር ባይበልጡ መልካም ነው፡፡ በሚተዋወቁና በቀላሉ በአንድ በተወሰነ ጊዜ ሊገናኙ የሚችሉ ቢሆኑ ይመረጣል፡፡ ግን ማንም በአንድ ቡድን ውስጥ ለመሳተፍ ለሚፈልግ ሰው ቡድኖቹ በራቸው ክፍት መሆን ይኖርበታል፡፡

የሚቋቋሙት አነስተኛ ቡድኖች ስም ቢኖራቸው ይመረጣል፣ አለበለዚያ የእከሌ ቡድን መባላቸው ላይቀር ይችላል፡፡ ለመጽሐፍ ቅዱሱ ኮሌጁ የቡድኑን ስም ማስታወቅ፣ በስሩ ያሉትን ስሞች ዝርዝር ማሳወቁና የት ወይም በስንት ሰአት እንደሚሰበሰቡ ማሳወቁ አስፈላጊ ነው፡፡ እንደሁኔታውና እንደተማሪዎች ጥያቄዎች አስተማሪዎች በአነስተኛ ቡድኖች ሊሳተፉ ይችላሉ፡፡

አነስተኛ ቡድኖች አስተባባሪዎች በፈቃደኝነት ላይ በተመሰረተ መልኩ የኮሌጁን አንዳንድ አስተዳደራዊ ስራዎች፣ የተማሪዎችን መዋጮዎችና የተማሪዎች ምረቃዎችን ያስተባብራሉ፡፡